Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የህፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት መስፈርት እና አሰራርለመወሰን የወጣ መመሪያ በይፋ ስራ ላይ ዋለ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መመሪያ ቁጥር 1084/2017 ረቂቅ ግብዓት በማሰባሰብና የመጨረሻ ሰነድ ዝግጅት ለአስተያየት ከፍትህ ሚኒስቴር አስተያየቶችን መቀበል በተሰጠ አስተያየት መሰረት አስተካክሎ በመላክና በማስመዝገብ ዛሬ በይፋ ስራ ላይ አውሏል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቴ ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ለመደገፍ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት በመንግስት የስራ ቦታዎች፣ በግል ድርጅቶች፣ በማህበረሰብ አቀፍ እና በሌሎች ዓይነቶች የማስፋፋት ስራ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ አካል በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት ማስፋፋትና ማጠናከር የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎች ጤናማ አካላዊ፣ አዕምሮአዊ እና ማህበራዊ እድገት እንዲኖራቸውና ጠንካራ የስብዕና መሰረት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለውም ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት የሚኖራቸውን ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎች በመረዳት በመንግስት የስራ ቦታዎች፣ በግል ድርጅቶች እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት እንዲተገበር ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እስካሁን በተሰሩ የክትትል፣ ድጋፍና ግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በ2017 ዓ.ም በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት ማለትም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከተጠሪ ተቋማት፣ ከመንግስትዩኒቨርሲቲዎች እና ከፌዴራል መንግስት የልማት ድርጅቶች በተሰበሰበ መረጃ መሰረት 176 ተቋማት አገልግሎቱን በማስጀመር ከ4100 በላይ ህጻናት ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉ
ተደምጠዋል፡፡ ምንም እንኳን የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት በስፋት እንዲቋቋሙ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ ቢሆንም የአገልግሎቱን ተደራሽነት ከማስፋት ባለፈ በማዕከላቱ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁና የህጻናትን መብት እና ደህንነት ያረጋገጡ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚረዳ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሰረት በማድረግ የህጻናትማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት መመሪያ እና ዝርዝር የአገልግሎት መስጫ መስፈርት አዘጋጅቶ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡ የህፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት መስፈርትን አሰራር መመሪያው ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
