ለክልሉ ሴት የምክር ቤት አባላት በሥርዓተ-ፆታ እና አካቶ ትግበራ ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የአፋር ክልል ሴት የምክር ቤት አባላት ዛሬ በሥርዓተ-ፆታ እና አካቶ ትግበራ ዙሪያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተጠናቋል።

ሥልጠናው የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የሴቶችን አካታችነት በማረጋገጥ የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማጠናከር ያለመ ነው። የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ ኮከሱ፣ ቢሮው የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ የልምድ ልውውጦችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው፣ የምክር ቤቱ አባላትም የሴቶችን ተጠቃሚነት በተግባር በማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ብለዋል። በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደገፉ ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ ሥልጠናው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከፍ ከማድረጉ ባሻገር የምክር ቤቱ አባላት የመፈፀምና የመወሰን አቅማቸውን በመጠቀም እንዲሰሩ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያለውን የአካቶ ትግበራን በተመለከተ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እንዲሰሩ የሚያግዛቸው መሆኑንም ገልፀዋል። ሥልጠናው የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን፣ የክልሉ ሴት የምክር ቤት አባላት ከ8ኛ መደበኛ ጉባዔ በኋላ የተካሄደ ነው።

 

Please follow and like us: