ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍልሰት ተመላሽ ሴቶችንና ታሳቢ ፍልሰተኞችን ለማብቃት እየተተገበረ ያለው  ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል – ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዴቨሎፕመንት ኤክስፐርትስ ሴንተር (DEC) ጋር በመተባበር ከፍልሰት ተመላሽን መልሶ ለመቋቋምና ታሳቢ ፍልሰተኞችን አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ህጋዊ የውጭ ስራ ስምሪት ዙሪያ ግንዛቤያቸውን ለማጎልበት የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት በመፈራረም እየተገበረ ያለውን ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

‎ሚኒስቴሩ ከዴቨሎፕመንት ኤክስፐርትስ ሴንተር (DEC) የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 1500 የሚሆኑ ከፍልሰት ተመላሾችንና ታሳቢ ፍልሰተኞችን ለማብቃት በትኩረት እየሰራ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

‎‎በመድረኩ ላይ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደምሴ እና በፕሮግራሙ አስተባባሪ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብና ውይይት በማድረግ የወደፊት አቅጣጫና የስራ መመሪያ ተሰጥቷል። ‎በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በንግግራቸው፥ መንግስት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ለመግታት በተጨማሪ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ተጎጂ የሆኑና ተጋላጭ ፍልሰተኞችን ለመደገፍና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ይህም ተግባር የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
‎እስካሁን ያለው የፕሮጀክት አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እየሄደ እንደሚገኝ በመጠቆም በቀሩት ጊዜ ፕሮጀክቱ የተያዘለትን ግብ እንዲያሳካ በትኩረት መሰራት እንዳለበት እና ለዚሁ ስኬትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጧል።

Please follow and like us: