Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሴልኮን ፋውንዴሽን በግብርና ዘርፍ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተነደፈውን ፕሮጀክት በተስማሚ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በህንድ የሴልኮን/SELCON/ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሀሪሽ ሀንዴን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የውይይቱ ዋና አጀንዳ በግብርና ዘሮፍ የሚተዳደሩ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተነደፈውና “Women in Agriculture” የተሰኘውን ፕሮጀክት በተስማሚ ቴክኖሎጂ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ ነው። በውይይቱ ወቅትም፥ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን የስራ ጫና ማቃለል፣ ምርታማነትን ማሳደግና የምርት ብክነትን መቀነስ በሚያስችሉ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች መደገፍ ይገባል ብለዋል። ለዚህም ሚኒስቴሩ በገጠር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በግብርና የሚተዳደሩ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት ያለመ ፕሮጀክት በመቅረፅ በሙከራ ደረጃ በጋምቤላ ክልል ለመተግበርና በሌሎችም አካባቢዎች ለማስፋፋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ለማሸጋገርም ሴቶችን አካታች ያደረገ የፋይናንስ ስርዓት ለማጠናከርና በፓሊሲ ጭምር እንዲደገፍ ለማስቻል ከፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአጋርነት ይሰራል ብለዋል። መሠረቱን ህንድ ያደረገው የሴልኮን/SELCON/ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሀሪሽ ሀንዴን በበኩላቸው፥ በህንድ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና በግብርና የሚተዳደሩ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተሞክሮ መኖሩን ጠቁመው ይህን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና ለመተግበር ፍቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ በሚኒስቴሩ በኩል ለመተግበር የታቀደውን ፕሮጀክትም ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። በቀጣይም የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም የቀረበውን የፕሮጀክት ሃሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጋራ ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ተስማምተዋል።
