Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የሚተገብረውን የአምስት ዓመት መርሃ-ግብር በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ተጠየቀ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑትን ዶ/ር አቡበከር ካምፖን በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለፁት ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ በሚተገብረው የአምስት ዓመት መርሃ-ግብር ተገቢውን ድጋፍ ለተገቢው ህፃን ተደራሽ በማድረግ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ መሆን አንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ይህም የህፃናትን ችግር ተጋላጭነትና ለችግር ተጋላጭ የሚያደርጓቸው ምክንያቶችን በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ እንደሚሆን ጠቁመዋል።በተጨማሪም ድርጅቱ የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱና በዚህ ወቅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚያከናውናቸው የማደጎ ስርዓትን የማዘመን፣ አማራጭ የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ አገልግሎትን የማስፋፋት እንዲሁም እየተሠራ ያለውን የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ስራንም እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ዶ/ር አቡባካር ካምፖ በበኩላቸው፥ ዩኒሴፍ የህፃናትን እና የሴቶችን መብት ለማሻሻል፣ የህፃናት ህልውና፣ ልማት እና ጥበቃ ለማረጋገጥ የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን ለመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከእ.ኤ.አ 1952 አንስቶ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራም ይገኛል።
