Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀና ህጋዊ የፍልሰት መንገድ እንዲመርጡና በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም ሰርተው እንዲለወጡ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል – ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ህጋዊ መንገድን የተከተለ ፍልሰትን ለማበረታታት በተዘጋጀው ብሔራዊ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂና ተያያዥ የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል።
በስልጠና መርሐ-ግብሩ ላይ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ ፍልሰት አለም አቀፋዊ ይዘት ያለውና ኢትዮጵያም ዋነኛ መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር መሆኗን አንስተዋል። ፍልሰት ተፈጥሯዊም ህጋዊም መብት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ መንግስት የፍልሰት ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የዜጎችን ደህንነትና ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅና መደበኛ የሆኑ የፍልሰት መንገዶችን የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ከፍልሰት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታትና የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመታደግ ብሔራዊ ምክር ቤት መቋቋሙን፣ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘቡ የተለያዩ የአሰራር ማዕቀፎች ተቀርፀው በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ገልፀዋል።
ማዕቀፎቹ እንዲታወቁና እንዲተገበሩ፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት እንዲሰጡና በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እንዲመዝገብ ለማስቻል ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ግንዛቤ በማሳደግ ዜጎች ህጋዊና አስተማማኝ መንገዶችን ብቻ እንዲጠቀሙ ማበረታታትና ትክክለኛ መረጃ መስጠት ከመዋቅሩ በስፋት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል። ታሳቢ ፍልሰተኞችም ተስፋ እንዲሰንቁ፣ በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ችግር ከመከሰቱ በፊት ድርጊቱን ለመከላከል፣ የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃን ለማረጋገጥ፣ የመረጃ ስርዓቱን ለማዘመን፣ ጥናትን መሰረት ያደረጉ የፓሊሲ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ፣ የቅብብሎሽ ስርዓቱ የተሳለጠ እንዲሆንና በህገወጦች ላይም አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ለማስቻል የጀመረውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልፀዋል። ስልጠናው በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ ከሲዳማ፣ ከድሬደዋ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
