በማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችና በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን መካከል ያለውን ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ

ይህ የተገለፀው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 ጎን ለጎን እየተካሄደ ባለው የፓናል ውይይት ወቅት ነው፡፡
‎በውይይቱ ላይ የተገኙት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለጹት፥ በማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችና በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ፕሮግራሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር አለብን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ፕሮግራሞቹ ለታሰበለት አላማ ከማዋል ባሻገር የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በየደረጃው መመዝገቡን በማረጋገጥ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን በኩል አብዛኞቹን ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመድረስ ይረዳናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም ላይ በፓናል ውይይት የተሳተፉት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በብሔራዊ የማህበራዊ ምዝገባና በጤና ስርአት ማሻሻያ ላይ አዳዲስ እድሎችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አገራዊ የመረጃ ሥርዓቶችን በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥ እና ተጠያቂነትን ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
‎በዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትም የእያንዳንዱ ዜጋ ጥያቄዎች በልዩ ሁኔታ ተለይተው ከጤና እና ማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ጋር እንዲገናኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ፣ ዲጂታል ክፍያዎችና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን እና የሴፍቲኔት ተጠቃሚነት በግልፅ እና በቀጥታ ለሚያስፈልገው ለቤተሰብ እንዲደርሱ እያስቻሉት ሲሆን ይህም ፍትሃዊነትን እና በስርዓቱ ላይ መተማመንን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡ የፎረሙ ዓላማ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎችን በማሳተፍ የኢትዮጵያን የሰው ሀብት ልማት ለማሻሻል የሚያስችሉ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ላይ ለመወያየት መሆኑ ተገልጿል።

Please follow and like us: