Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የፍልሰት ተጋላጭነት ለመከላከልና ተጎጂ ፍልሰተኞችን መልሶ ለማቋቋም ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።- ክብርት ሁሪያ አሊ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞማ የሚገኙ የሱዳን ተመላሽ ዜጎችን ወደ ማህበረሰቡ ማቀላቀልና መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግና በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ምክክር ተካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ሁሪያ አሊ በዚሁ ጊዜ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በተፈጥሮና በሠው ሠራሽ ምክንያቶች ተገደው የሚፈናቀሉ ፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር መሆኗን ገልፀዋል። ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፥ ተመላሽ ዜጎች በመተላለፊያና መዳረሻ አገራት የደረሰባቸውን አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከግምት ውስጥ ያስገባ ድጋፍ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር መዘርጋትና መተግበር ያስፈልጋል። የፍልሰት ተጋላጭነት ለመከላከል፣ ተጎጂ ፍልሰተኞችን መልሶ ለማቋቋምና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ሁላችንም ድርሻ አለን ብለዋል። ጠንካራ የስራ ባህል ያላቸው፣ በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችንና ምቹ ሁኔታዎችን የሚጠቀሙ ከራሳቸው አልፎ አገር ለመለወጥ የሚተጉ ወጣቶችን ለማፍራት መተጋገዝ አለብን ብለዋል። ሚኒስቴሩ ወደፊትም በአስከፊነቱና መፍትሔው ዙሪያ እያካሄደ ካለው የግንዛቤና ንቅናቄ ስራ ባሻገር የፍልሰት ተመላሾች የማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ወደ ማህበረሰቡ ለማቀላቀልና መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) በዞኑ ባሉ ስድስት ወረዳዎች ለተጎጂዎች መረጃ ሰጪ ዴስኮችን እንዲጠናከሩ እንዲሁም ተመላሾች እንዲቋቋሙ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው ለስኬታማነቱ የክትትል ስራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ከመደበኛ ኑሯቸው በግዳጅ ተፈናቅለው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎች ድጋፍ አግኝተው ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት፣ ሊኖር ስለሚገባው ቅንጅታዊ አሰራር እና ተያያዥ ጉዳዮች መምከርና የቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በመድረኩ የሲቪክ ማህበረሰቦች፣ የክልሉ የስራ ሃላፊዎች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፍትህ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
