ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውልና ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ሁላችንም በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል- ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና ላይት ፎር ዘ ወርልድ ጋር በመተባበር በረቂቅ ደረጃ በተዘጋጀው ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ላይ የመጨረሻ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

‎‎በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች የሚያስከብሩ አለም አቀፍ ስምምነቶች በመቀበል፣ ደጋፊ የአሰራር ማዕቀፎችና አደረጃጀት በመዘርጋት ለተፈፃሚነቱ በርካታ እርምጃዎች እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል።‎
‎ፖሊሲው ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር ብሎም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በተጨማሪም የተጠያቂነት ብሎም የክትትልና ድጋፍ ስርዓት ለመዘርጋት፣ የአለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈፃሚነት ለማፅናት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት እንዲሁም ወጥ የሆነ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የፖሊሲ ማዕቀፉ መኖር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

‎‎ፖሊሲው ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውልና አካል ጉዳተኞችም የልማት ተካታችና የእኩል ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ሆኖም እንደሀገር አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ተግባራትን በአንድ ተቋም ብቻ በሚደረግ ጥረት ማሳካት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል። በዘርፉ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀው፥ ፖሊሲው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

 

‎ለፖሊሲው ዝግጅት ግብዓት በመስጠት፣ በቴክኒክና በፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርጉ ለቆዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል። ‎የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ ማህበሩ አካል ጉዳተኞች ክብራቸው፣ መብታቸውና ደህንነት ተጠብቆ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲረጋገጥና አካታች ማህበረሰብ እንዲፈጠር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
‎
‎

Please follow and like us: