መንግስት አካል ጉዳተኞችን የልማት ተካታችና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ከክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እናድርግ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
‎በመርሐግብር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ አካል ጉዳተኞች አስቻይ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ከራሳቸው ባለፈ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሰፊ አበርክቶ እንዳላቸው ገልፀዋል። ‎ለዚህም መንግስት አካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው በተጠበቀበት አግባብ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉና ከውጤቱም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የአካል ጉዳተኞችን መብት ማስከበር፣ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግና ማብቃት የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

‎መንግስት በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ዋና መገለጫው አካታችነት መሆኑን ጠቅሰው ወደፊትም ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር ብሎም የተሻለ የልማት ተካታችና ተጠቃሚነት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል። ‎CBM’ን ጨምሮ ለጋሾች እና የልማት አጋራት እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነው፥ ድጋፉ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

 

‎‎የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ጉጆ፤ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የሲ ቢ ኤም/CBM/ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ሄይኮ ቮሞብስ በበኩላቸው፥ አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ማለፍና ህይወታቸውን በዘላቂነት መለወጥ እንዲችሉ ማብቃትና አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፤ ለዚህም በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
‎

Please follow and like us: