የታዳጊ ሴቶች ልዩ ፍላጎቶችን በመረዳት የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች በተባበረ ክንድ መፍታትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከሁላችንም ይጠበቃል- ክብርት ሂክማ ኸይረዲን

‎አለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶቾ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ “ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።

‎በዓሉን አስመልከተው በቪዲዮ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ኸይረዲን፣ ቀኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የታዳጊ ሴቶች ህልምና እምቅ ችሎታ እውን እንዲሆን መሰረት የተጣለበት ቀን መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ‎ዕለቱን ስናከብር ታዳጊ ሴቶች በመንገዳቸው የሚያጋጥሟቸውን ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በመፍታት ለነገ ብቁ የሆኑ የሀገር ተረካቢ ሴቶችን ለማፍራት ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት በተግባር ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ታዳጊ ሴቶች አስቻይ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው የለውጥ ሀይል፣ የነገ ሀገር ተረካቢ፣ ሀገር አበልጻጊና አሻጋሪ የዘርፈ-ብዙ ዕውቀት ባለቤት እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

‎‎በመሆኑም የዛሬ ስራችን ልጃገረዶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲገነዘቡ እና ለህብረተሰቡ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ብሎም መሰናክሎችን አንዲሻገሩ በማድረግ በሀገር ግንባታ ውስጥ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማብቃት ያስፈልጋል ብለዋል ‎እንዲሁም የታዳጊ ሴቶች ልዩ ፍላጎቶችን በመረዳት የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶችን በተባበረ ክንድ መፍታትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

ለታዳጊ ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ሚኒስቴሩ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሚኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ለኮከበ ጽብሃ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እና ለእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ለተሳተፉ ተማሪዎች የታብሌት ሽልማት አበርክቷል።
‎
‎በተጨማሪም ለትምህርት የሚያግዙ የተለያዩ መፅሃፍቶች እና የንህጽና መጠበቅያ ድጋፍ አድርጓል።
‎
‎በዓሉ ሲከበር፥ ታዳጊ ተማሪዎች የፈጠራ ክህሎቶቻቸውንና የማነቃቅያ ስራዎቻቸውን ለእንግዶች አሳይተዋል።

Please follow and like us: