ሚኒስቴሩ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የሚተገብራቸውን ቀጣይ ስራዎች ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ጠየቀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ(UNICEF) ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማንና ልኡካን ቡድናቸውን በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለፁት፥ ከዚህ ቀደም በተወያዩት መሰረት ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ በሚተገብረውን የአምስት ዓመት መርሃ-ግብር ከሚኒስቴር መ/ቤቱ እቅድ ጋር ለማጣጣም መስራቱን አድንቀው አሁንም ቀጣይ ስራዎች ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ጠይቀዋል::ይህም የህፃናትን ችግር ተጋላጭነትና ለችግር ተጋላጭ የሚያደርጓቸው ምክንያቶችን በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ እንደሚሆን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የህጻናት መብቶች ድንጋጌዎችን ተቀብላ በማጽደቅና የሕግ አካል በማድረግ የሕጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን፣ ፕሮጀክቶችንና የማስተግበሪያ ስልቶችን በመንደፍ እየተገበረች መሆኑን ገልፀው ዩኒሴፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማን በበኩላቸው፥ ዩኒሴፍ በዚህ ወቅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚያከናውናቸው የማደጎ ስርዓትን የማዘመን፣ አማራጭ የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ አገልግሎትን የማስፋፋት እንዲሁም እየተሠራ ያለውን የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ስራን እንደሚደግፍ ገልፀዋል፡፡

Please follow and like us: