Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአእምሮ ጤናን ችግር መፍታት ፍትሃዊ፣ ሁሉን ያካተተና ተደራሽ እንዲሁም ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል -ክብርት ሁሪያ አሊ
ቦርን አጌን የአዕምሮ ጤና እንክብካቤና ማገገሚያ ማዕከል የአእምሮ ጤና ቀንን ምክንያት በማድረግ የዉይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት የአእምሮ ጤና የሰዎች ጤናና ደህንነት መሠረታዊ አካል መሆኑን ገልፀዋል።ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአእምሮ ጤና የሕክምና ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ የማኅበራዊ ጉዳይ መሆኑንም ይገነዘባል። የአእምሮ ጤና ችላ ሲባል፣ ቤተሰቦች ይሠቃያሉ፣ ማኅበረሰቦች ይዳከማሉ፣ እንዲሁም የሀገር ምርታማነት እንደሚቀንስ ተናግረዋል። በመሆኑም፣ የአእምሮ ጤናን ችግርን መቅረፍ ፍትሃዊ፣ ሁሉን ያካተተና ተደራሽ እንዲሁም ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልፀው ችግሩን የደረሰባቸውን ሰዎች ድጋፍና ክብካቤ በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ጥበቃ፣ በማኅበራዊ ደህንነትና ሁሉን አቀፍ ልማት ረገድ ጉልህ እርምጃዎችን ወስዳለች እየወሰደችም እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የአእምሮ ጤናንና የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎቶችን በማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ውስጥ በሰፊው ለማካተት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ማኅበረሰብ አቀፍ የማገገሚያና የምክር አገልግሎቶችን ማጠናከር፣ ተቋማዊ እንክብካቤና መልሶ የማቋቋም ፕሮግራሞችን ማስፋፋትና ማሳደግ ፣ሁሉን አቀፍ የማገገሚያና የፈውስ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ቦርን አጌን ያሉ ድርጅቶችን መደገፍና ማጠናከር፣ መገለልንና መድልዎን ለመዋጋት ሀገር አቀፍ ግንዛቤንና ቅስቀሳን ማስተዋወቅ ይጠቀሳሉ፡፡
