Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ከችግር ተላቀው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ ጥሪ ቀረበ
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐግብር የሚመለከታቸው የሥራ መሪዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሕጻናት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ አክብሯል።
በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ “የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ የተገኙ ሕጻናት በመጫወቻ ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። በመድረኩ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ቀርቧል። የተማሪዎች የጥያቄ እና መልስ ውድድር ተካሄዶ ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ለበዓሉ ትብብር ላደረጉ አካላትም ዕውቅና ተሰጥቷል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ በዓሉ በየደረጃው በተለያዩ ዝግጅቶች በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች እና በዞኖች ሲከበር ቆይቷል ብለዋል።
ይህ በዓል በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሠሩ ሥራዎችን በማጠናከር ሕጻናት ደኅንነታቸው፣ ጤንነታቸው እና አካላዊ ብቃታቸው የተጠበቀ ኾነው እንዲያድጉ ብዙ ሥራዎች እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል። ሕጻናት የዴሞክራሲ ሥርዓት መብታቸውን እንዲለማመዱ በሕጻናት ፓርላማ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለሕጻናት ጤናማ እና ለኑሮ ምቹ፣ ተስማሚ አካባቢ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መሠራት ስላለበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሕጻናት የአንድ ሀገር የወደፊት ተስፋ እና ሀብት ናቸው ብለዋል። ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ላይ መሥራት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በማኅበራዊ ኑሮ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡
የሕጻናት ቀን ሁነቶች ሕጻናት ተሰባስበው በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት በመሆኑ በክልሉ ለሁለት ወራት በግንዛቤ ማስጨበጫ እና በተለያዩ ሁነቶች እስከ ወረዳ ድረስ ሲከበር ቆይቷል ብለዋል፡፡ የሕጻናት ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲሁም የመጫወቻ ቦታዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በየአካባቢው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተሠርቷል ነው ያሉት። የሀገር ተረካቢ ሕጻናት ከችግር ተላቀው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ እና ሀገር ወዳድ ዜጎች እንዲሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቢሮው አስታውቋል።
