ከተማችንን በአፍሪካ ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ ለማድረግ በክብርት ከንቲባ ኢንሼቲቭ የተጀመሩ ተግባራትን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል

‎የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የዘንድሮውን የዓለም ሕፃናት ቀን በሃገራችን ለ20ኛ ጊዜ “የሕፃናት ጥበቃና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕፃናት!” በሚል መሪ ቃል ሕፃናትን፣ ወላጆችን፣ የሐይማኖት አባቶችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የማህበረሰብ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በልዩ ልዩ ሁነቶች በማክበር ላይ ይገኛል።

‎በዛሬውም ዕለት በሕፃናት መብት እና በጨዋታ የመማር ጠቀሜታ ዙሪያ ሰነድ በማቅረብ የፓናል ውይይት አካሂዷል። በፓናል ውይይቱ በልዩ ልዩ መልኩ ከሕፃናት ጋር የሚሰሩ ምሁራን፣ ኤክስፐርቶች፣ የሕፃናት ሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል። በመድረኩ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ባስተላለፉት መልዕክት ከተማችንን በአፍሪካ ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ ከተማ ለማድረግ በክብርት ከንቲባ ኢንሼቲቭ የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል ረገድ ቢሮው በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል። ለአብነትም የቀዳማይ ልጅነት ልማት ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች፣ የሕፃናት የልደት ምዝገባ ሰርተፍኬት፣ የሕፃናት የእንክብካቤ አማራጮችን በማጠናከር፣ የሕፃናት ተሳትፎን ለማሳደግ የሕፃናት ፓርላማን በማቋቋም እና ተስማሚ የሕፃናት ፍርድ ቤቶችን በማስፋፋት ረገድ አበረታች ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

‎ሕፃናት ሀሳባቸውንና ስሜታቸውን በብዙ መልኩ መግለፅ እንዲችሉ ለማበረታታት ወላጆችም፣ መምህራንም እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማትም በትኩረት እንዲቀሳቀሱበት አሳስበዋል። ‎በመርሐግብሩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቀጣይም በየተሰማሩበት አውድ እና አግባብ በሕፃናት ተጠቃሚነት ዙሪያ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልፀዋል።
‎

Please follow and like us: