Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የፈንጂ አደጋ ስጋትን ጨርሶ ለማስወገድና የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም አጋር አካላት በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ
የፈንጂ አደጋ ስጋትን ጨርሶ ለማስወገድና የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም አጋር አካላት በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ጥሪ አቀረቡ።
የፈንጂ አደጋ ስጋትን ጨርሶ ለማስወገድና የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ሀብት ለማሰባሰብና አጋርነትን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ የማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ በግጭት ወቅትም ሆነ ግጭቶች ከቆሙ በኋላም በየቦታው የተጣሉና የወዳደቁ የጦርነት ቅሪቶች በተራዘመ ጊዜ በሰዎች ህይወትና በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን የበለጠ ተጎጂ እንደሚሆኑና ከአደጋው በኋላ ለተራዘመ አካላዊ፣ ስልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚዳረጉ ተናግረዋል። በመሆኑም የፈንጂ አደጋ ስጋቱ ጨርሶ እስኪወገድ ድረስ በቀጠናው የሚገኙ የህብረተስብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን አካባቢውን ማፅዳት፣ የተጎዱትን መልሶ ማቋቋም፣ የአካል ድጋፍ ማቅረብና የክህሎት ልማት ፕሮግራሞችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናት በማድረግና ፈንጂን በማስወገድ፣ በአካል ጉዳተኞች መብት፣ በማህበራዊ ጥበቃ፣ በጤናና በመልሶ ማቋቋም ዙሪያ በተበታተነ መልኩ የሚሰሩ አካላትን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ለጋሽ ድርጅቶች እና የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የፈንጂ አደጋ ስጋትን ጨርሶ ለማስወገድና የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራት ውጤትማ ለማድረግ በትብብርና ቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
