በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሚዘጋጀው 70ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ እንደ አህጉር አንድ አይነት ድምፅ ለማሰማት ያግዛል የተባለው የሚኒስተሮች ቅድመ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው።

በየአመቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅ/ቤት ኒውዮርክ ለሚካሄደው 70ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ (Commission on the Status of Women) የአፍሪካን ጉዳዮች በመዳሰስ አንድ አይነት ድምፅ ለማሰማት ያግዛል የተባለው የሴቶችና ማህበራዊ፣ የስርዓተ ፆታና ወጣቶች ሚኒስትሮችን ያሳተፈው ቅድመ ውይይት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በመካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት የዘንድሮ ቅድሚያ የሚሰጠው ጭብጥ “ሁሉንም ሴቶችና ልጃገረዶች የፍትህ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ማጠናከር፣ አካታችና ፍትሃዊ የሕግ ሥርዓቶችን በማስፋፋት፣ አድሎአዊ ሕጎችን፣ ፖሊሲዎችንና ልምዶችን በማስወገድ እና መዋቅራዊ እንቅፋቶችን መፍታትን ጨምሮ ለሁሉም ሴቶችና ታዳጊ ሴቶች የፍትህ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ማጠናከር መሠረታዊ ጭብጥ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።  በመላው አፍሪካ፣ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ እንቅፋቶች ይህንን መሠረታዊ መብት እንደሚያደናቅፉ ገልፀው አድልዎ የሚፈጥሩ ሕጎች፣ በማስፈጸም ላይ ያሉ ክፍተቶች፣ የተገደበ የተቋማዊ አቅም እና ሌሎች ሥር የሰደዱ ማህበራዊ ደንቦችን የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የፆታ እኩልነትን እና የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቁመው ሕገ መንግሥቱ ለሴቶች እኩል መብቶችን ማስቀመጡን ገልፀዋል። በተጨማሪም CEDAW እና የማፑቶ ፕሮቶኮልን ጨምሮ ቁልፍ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ ሰነዶችን በማፅደቅ የቤተሰብ እና የወንጀል ህጎቻችንን ጨምሮ አድሎአዊ ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ሰፊ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቁመዋል። የአፍሪካ ህብረትም በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም የተደረገ ስምምነት ታሪካዊ እና ለውጥ የሚያመጣ ኮንቬንሽንን ይዞ መምጣቱ ለውጡን ይበልጥ የሚያፋጥነው ይሆናል ብለዋል። ይህንንም ለማገዝ አባል ሀገራት ኮንቬንሽኑን እንዲፈርሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በሴቶች ልማት ላይ ትኩረት ያደረገና COmmission ON THE STATUS OF WOMEN (CSW) በመባል የሚታወቀው ዋና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎች የሚሳተፉበት የጉባኤ መድረክ በየአመቱ እንደሚካሄድ ይታወቃል። ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ በ2025 ለሚካሄደው 70ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ አፍሪካን በመወክል የኮሚቴው አባል ሆና መመረጧ ይታወሳል፡፡ ውይይቱ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነትና በ ተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ፆታና ሴቶችን ማብቃት ድርጅት (un women) ድጋፍ ተከናውኗል ።

Please follow and like us: