Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ለዜጎች የማህበራዊ ጥበቃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት የአለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚደግፍ ቃል ገባ።
ይህ የተገለፀው በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በኢትዮጵያ የአለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ከሆኑት ዶ/ር ሙቲንታ ሃምባዪ በተወያዩበት ወቅት ነው።

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ላይ ፖሊሲና እና ስትራቴጂውን ከማዘጋጀት ጀምሮ በኩል በኮቪድ-19 ወቅት ለከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (UPSNP) ምላሽ በመስጠት ላበረከተው አስተዋፅኦና አጋርነት አመስግነዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል አንዱ ለዜጎች የማህበራዊ ጥበቃ ተደራሽነትን ለማስፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የመንግስት እና የግል ዘርፎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን እና ስልቶችን በማዘጋጀት፣ ድሆች እና ተጋላጭ ቡድኖች ከአገር አቀፍ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ ላይ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል የአለም የምግብ ፕሮግራም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ላይ መረጃን ለመሰብሰብ፣ ለማደራጀት እና ለመተንተን ዘመናዊ ስርዓቶችን ማዘጋጀት ላይ ትኩረት በማድረግ ማህበራዊ ድጋፍን፣ የትምህርት ቤት ምገባንና እና የጤና መድህንን ጨምሮ ጠንካራና ምላሽ ሰጪ ስርዓቶችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ለዚህም የአለም የምግብ ፕሮግራም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙቲንታ ሃምባዪ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ለዜጎች የማህበራዊ ጥበቃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁና ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል የገቡ ሲሆን በተጨማሪም በሌሎች የትብብርና የቅንጅት ስራዎችን በጋራ ለመስራት ያላቸውን ተነሳሽነት ገልፀዋል።
