የ2018 ዓ.ም የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ጋር በጋራ በመሆን የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የአካል ጉዳተኞች ቀን ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ፤ Fostering disability inclusive societies for advancing social progress! ” ወይም “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት – ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት!” በሚል መሪ ቃል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተናጋጅነት በመቐለ ከተማ ህዳር 24/2018 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በድምቀት ይከበራል፡፡

የአለም የአካል ጉዳተኞች ቀንን በኢትዮጲያ ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት አንዱ ምክንያት እንደ ሀገር አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት፣ አካል ጉዳተኞችንም በትክክል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በየጊዜው ማስታወስ፣ ማረጋገጥና መከታተል ስለሚገባ ነው። በዚሁ ላይ ተመስርቶ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በየጊዜው ግንዛቤ በመፍጠር፣ ክፍተቶችን በማመላከት እና እንዲያሻሽሉ በማድረግ፣ አካል ጉዳተኞችን በሁለንተናዊ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል።

በ2018 ዓ.ም የአካል ጉዳተኞችን ቀን ዋነኛ ዓላማዎቹ

👉አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የዕኩል እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ለማቅረብ የሚያስችል ቅስቀሳ ለማድረግ፣

👉በዘርፉ በተለይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸውን አካላት ለማስገንዘብና አስፈላጊውን ኃላፊነት አንዲወጡ ለማስቻል፣

👉በውጤቱም መብቶቻቸው ተከብረው ተሳትፎአቸው እንዲያድግ ተገቢው ማሻሻያ እና ትግበራ እንዲደረግ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከመሪ ቃሉ እንደምንረዳው አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ የመገንባትን አስፈላጊነት የሚያስገነዝብ ነው፡፡

አካታች ማህበረሰብ የመፍጠር አንዱ እና ዋነኛው መገለጫ የአካል ጉዳተኞችን የእንቅስቃሴ ችግሮች መቅረፍ በመሆኑ ይህን መሰል የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሲቀጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትም በዛው ልክ ያድጋል ተብሏል። እንደ ሚኒስቴር መ/ቤት ምን ተሰራ?

👉የአካላዊ ተሐድሶ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከላትን በማጠናከር ረገድ አስተዋጽኦ ያለው የተሃድሶ የልህቀት ማዕከል (EPOC) በመንግስት ተገንብቶ ሥራ መጀመሩ ይህም የአካል ጉዳተኞችን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ረገድ ተጠቃሽ ሚና ይኖረዋል፤

👉ተቋማችንም በመመሪያ ቁጥር 896/2014 መሰረት የእንቅስቃሴ ውስንነትን ለማቃለል፣ ከቀረጥና ታክስ ነጻ የሆነ ተሸከርካሪን የማስገባት አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ5000 በላይ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፤

👉ይህንኑ አገልግሎት በማሻሻል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ ኦንላይን የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማሳደግ ተችሏል፡፡ ይህም ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል፡፡

👉 የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙና በማህበር ተደራጅተው ሁለንተናዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር እንዲችሉ በመደረግ ላይ ነው፡፡

👉ክልሎች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከህንድ ኤምባሲና ጃይፐር ፉት ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በአፋር ክልል ሎጊያ ሆስፒታል ለ260፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለ177 አካል ጉዳተኞች የአካላዊ ተሃድሶ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡

👉 የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በህግ በሚደገፍ አሰራር ለማገዝ እንዲቻል ልዩ ልዩ የህግ ረቂቅ ሰነዶች ጸድቀው ስራ ላይ እንዲውሉ በተቋማችን ለመንግስት የቀረበ ሲሆን ሂደቱ በክትትል ላይ ነው፡፡

በመጨረሻም በበዓሉ ቀን የሚደረገውን ድጋፍ ውጤታማ ለማድረግ ለዚህ በጎ ተግባር በቅንነት በመንቀሳቀስ ሁለገብ ጥረት ላደረጉ አካላት ክብርት ሁሪያ አሊ እና አቶ አባይነህ ጉጆ አመስግነዋል።

 

Please follow and like us: