የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተመድ በህፃናት ጥበቃ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴክሬተሪ ጀነራል የህፃናትና የትጥቅ ግጭት ልዩ ወኪል የሆኑት ሚስ ቫኔሳ ፍሬዘር እና ልዑካቸውን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
‎‎የስራ ሃላፊዎቹ ከህፃናት መብት፣ ደህንነትና ጥበቃ አኳያ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተመድ መካከል በተገባው ስምምነት መሠረት በሰሜኑ ክፍል በግጭት ምክንያት የተጎዱትን ህፃናት ከመርዳት አኳያ በተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች እና ቀጣይ ትብብሮችን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ‎የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ መንግስት በግጭት አውድ ውስጥ በህፃናት ላይ ተፈፅመዋል የተባሉትን የመበት ጥሰቶች በመለየት የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኛነት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል። ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ህፃናትን ጨምሮ ለአካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማገገምና መቋቋም እንዲችሉ ከዩኒሴፍ፣ ዩኤን ኤፍ ፒኤ እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የጋራ ፕሮግራሞች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

‎ጉዳዩን በተመለከተ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ አጥኚ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ ብሔራዊ አስተባባሪ አካል መሰየሙን፣ የማህበራዊ ሰራተኞች ተቀጥረው ሙያዊ ድጋፍ እንዲሠጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንዲሁም የህፃናት ጉዳይ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱንና አሰራሩን ዲጂታላይዝ እየተደረገ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ አንስተዋል። ‎ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት የአንድ ማዕከላትና ጊዜያዊ ማረፊያዎችን በማቋቋምና በማጠናከር የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገና በግጭት ምክንያት ከወላጆቻቸው የተለዩ ህፃናትንም የማቀላቀል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
‎

Please follow and like us: