በሰላም እጦት ምክንያት ዜጎች ለከፋ ማህበራዊ ችግር እና ለአካል ጉዳት የሚዳረጉበትን ሁኔታ ማስቀረት ይኖርብናል _ክብርት ሁሪያ አሊ

በሀገራችን ለ 33ኛ ጊዜ የተከበረውን አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ በመቐለ ከተማ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በፊት መከላከልን መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በውይይትና በምክክር ችግሮችን በመፍታት ግጭቶችን በማስወገድ የሚደርሰውን የዜጎች ለችግር ተጋላጭነት እና የአካል ጉዳት ማስቀረት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማምጣት ለውይይትና ለምክክር ሁሌም ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ከሰላም ሊገኝ የሚችለው ትሩፋት በመረዳት በሰላም እጦት ምክንያት ዜጎች ለከፋ ማህበራዊ ችግር እና ለአካል ጉዳት የሚዳረጉበትን ሁኔታ ማስቀረት ይኖርብናል ሲሉ ተደምጠዋል። ስለሆነም ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ እየፈታን በዛውም አካል ጉዳትን በማስቀረት ተገቢውን መፍትሄ በምክክር ልናመጣ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የጊዚያዊ አስተዳደሩ ማህበራዊ ጉዳይና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረስላሴ ታረቀኝ በበኩላቸው ሁሉም አካል ጉዳተኞች የጤና፣ የትምህርት እንዲሁም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነታቸው ሊማረጋገጥ በመስራት ላይ እንዳለ ጠቅሰዋል። “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት – ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት!” በሚል መሪ ቃል በመቐለ ከተማ የተከበረው የዘንድሮ የአካል ጉዳተኞች ቀን ቀጣዩን ክብረ በዓል ለማክበር ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋንጫውን ተረክቧል። የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርም በዝግጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት ዕውቅናና ምስጋና በመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል።

Please follow and like us: