Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የቀደማይ ልጅነት ፕሮግራም ልማትን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና ማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶችን የስራው ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በቀደማይ ልጅነት እንክብካቤ ዙሪያ ስራዎችን ለማስጀመርና ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ከሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር ኢብራሂም ኡስማን፣ የክልሉ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ፣ የጤና ቢሮ ኃላፊ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተካሂዷል።
የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይረዲን በሀገር አቀፍ ደረጃ የቀደማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር በተጨማሪ ማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶችን የስራው ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ከሴቶችና ማህበራዊ ሴክተር በተጨማሪ በዋነኝነት ጤና፣ ትምህርት፣ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮዎች እና መሰል ባለድርሻ አካላት ታች ካለው መዋቅር ጋር በመቀናጀት፣ የእቅድ አካል በማድረግ፣ የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበርና በባለቤትነት በማሳተፍ እና የክትትልና ግምገማ ስርዓትን በማጠናከር ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው ትምህርት ተቋማት አሉን ነገር ግን ያሉትም ቢሆኑም ለህጻናት መጫወቻ ስፍራ የላቸውም ስታንዳርዱን የተከተሉም አይደሉም ነገር ግን ይህንን የማሳካት ፍላጎትም ተነሳሽነትም አለን ብለዋል። ለዚህም ጠንካራ የክትትል እና የግምገማ ስርአት ዘርግተን በተቀናጀ መንገድ ተባብረን በመስራት ላይም እንገኛለን፤ በቀጣይም አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለውም በቀጣይም ማንኛውም በክልሉ የሚሰሩ ስራዎች ትውልዱን ያማከለ እንዲሆን ለማስቻል ስትሪም እና ቴክኒካል ኮሚቴ በማዋቀር የእቅድ አካል በማድረግ ኃላፊነት እንወስዳለን በማለት ገልፀዋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱም በሰው ልማት ግንባታ እና ትውልድን የማበልፀግ ስራው ላይ የክትትል እና ግምገማ ስርዓት በመዘርጋት ከክልሉ ጋር በጋራ እንዲሰራም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል። በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ እንዲሁም በክልሉ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት ተደርጓበታል።
