Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የቤተሰብ ኢኮኖሚን ለማጠናከር የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት መተባበበርና መደገፍ እንዳለባቸው ተገለፀ
የቤተሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት ላይ በቅንጅት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ የማህበረሰብና የሀገር መሰረት የሆነው ቤተሰብ ወሳኝ ሚናዎቹን በሚገባ መወጣት እንዲችል ተገቢውን ጥበቃ ሊያገኝና ደህንነቱ በዘላቂነት ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል። የቤተሰብን ደህንነትና የተረጋጋ ኑሮ ከሚያውኩ መንስኤዎች መካከል ድህነት ዋነኛው መሆኑንና ይህም የቤተሰብ መውደቅን በማስከተል በማህበረሰብና በሀገር ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር አንስተዋል። የቤተሰብ ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሃላፊነት አይደለም ያሉት ክብርት ሁሪያ ቤተሰብ ከድህነት ተጋላጭነት ተላቆ ወደ አምራችነት እንዲሸጋገር፣ ከራስ ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ሚናውን እንዲወጣና ለትውልድም የሚሻግር ጥሪት ማፍራት እንዲችል የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራትና መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል::
በተጨማሪም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያሉ የፖሊሲ ችግሮችን መቅረፍ፣ የፋይናንስ ተቋማት ሁሉንም ዜጎች በአካታችነት እንዲያገለግሉ ማስቻል እንዲሁም የገጠር የስራ ፈጠራ እና የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ለቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ድርሻው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ የቤተሰብን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀው ጥረቱ እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡና እንዲደግፉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
