Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የፋይዳ መታወቂያ የሴቶችንና ህፃናትን የመታወቅ መብትና የሰብዓዊ መብት ከማጎልበት ባሻገር የዲጂታል ንቃተ ህሊናንም እንደሚያጎለብት ተጠቆመ
”ፋይዳ ለሴቶች” የምክክርና የንቅናቄ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል መታወቂያ ብቻ ሳይሆን ለሴቶችና ህፃናት መብት መከበር ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። የፋይዳ መታወቂያ የሴቶችንና ህፃናትን የመታወቅ መብትና የሰብዓዊ መብት ከማጎልበት ባሻገር የዲጂታል ንቃተ ህሊናንም እንደሚያጎለብት ጠቁመዋል። እንደ ሀገር 30 ሚሊዮን ሴቶችን የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ብሔራዊ ፋይዳ መታወቂያ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሁነኛ መሣሪያ በመሆኑ ሁሉም አካላት ለሀገራዊ ግቡ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና ተጋለጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታችነት ለማጠናከር፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት ዲጂታል መታወቂያው አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። በምክክርና የንቅናቄ መድረኩ ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ፣ የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መድረኩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባባሪ ጋር የተዘጋጀ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የሴት አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ይገኛል።
