Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሚዲያ ተቋማት ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ሁሉንም አስፈጻሚ አካላት በመጠየቅ እና ለችግሮች መፍትሔ በማመላከት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል – ክብርት ሁሪያ አሊ
በማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ የሚዲያ አካላትን ግንዛቤ ለማጎልበትና ተቀናጅቶ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ በጋራ ለመምከር የሚረዳ ከሚዲያ አካላት ጋር የስልጠናና የምክክር መድረክ ተካሄዷል
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በንግግራቸው ሚኒስቴሩ በተለይ በማህበራዊ ዘርፍ የአረጋውያን፣ የቤተሰብ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ተመላሽ ዜጎች እንዲሁም ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በዋነኝነትም የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ፣ የሚስተዋሉትን የተሳሳቱ አመለካከቶች ለመለወጥ፣ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ፣ መብቶቻቸው በአግባቡ እንዲታወቁና እንዲከበሩ ለማስቻል፣ በየዘርፉ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በቅንጅተ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል
በየዘርፉ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም እንደሀገር ያሉት ማህበራዊ ችግሮች ሰፊ ውስብስብ መሆናቸውን ጠቁመው አካታች፣ ቀጣይነት ያለው ብሎም ተሻጋሪና ውጤታማ ስራ በመስራት የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥና ለማሻሻል ብዙ መሰራት ይጠበቅብናል ብለዋል። አክለውም ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚድያ ታቋማት ሁሉንም አስፈጻሚ አካላት በመጠየቅ እና ችግሮችን በማመላከት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያገኙና ሁለንተናዊ ተሳትፏቸው እንዲጠናከር የቤተሰብ ደህንነት እንዲጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ሚናው እንዲዘምን፣ ዜጎች በህገ ወጥ ስደት ምክንያት ተጎጂ እንዳይሆኑ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ በማህበራዊ ጥበቃ ጉዳይ፣ በአካል ጉዳተኞች ነባራዊ ሁኔታ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና ተመላሾች አያያዝ፣ በቤተሰብ ደህንነት እና በአረጋዊያን የድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ እንዲሁም በሚዲያ ተቋማት ሚና ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ማድረግ ተችሏል።
