‎እንደሀገር ያሉብንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የወገን ለወገን ትብብርን ማጠናከርና በጋራ መስራት እንደሚገባ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለጹ

‎ወገኔ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን የተመሰረተበት 25ኛ አመት የመታሰቢያ መርሐግብር ተካሂዷል::

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በመታሰቢያ መርሐግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተሰብ ሲጠናከርና ደህንነቱ ሲጠበቅ አብዛኛው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታሉ ብለዋል። ይሁንና ይህን በመንግስት አቅም ብቻ እውን ማድረግ አዳጋች መሆኑን ገልፀዋል። ‎የወገን ለወገን ትብብርን በማጠናከር በጋራ ከሰራን የማንንም እጅ ሳንጠብቅ እንደሀገር ያሉብንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ እንደሚቻል የወገኔ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን የ25 አመታት የስኬት ጉዞ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ‎ፋውንዴሽን በተለይም የህብረተሰብ መሰረት የሆነውን የቤተሰብን እና የአባላቱን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ከ371 በላይ ቤተሰቦችን በመደገፍ ላደረገው ብርቱ ጥረት አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል።

‎የፋውንዴሽኑ ልምድ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከዚህም በላይ አቅም እንዲፈጥር እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር በመስራት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች እንዲደርስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡‎‎መንግስት እንደ ወገኔ ኢትዮጵያዊያ ፋውንዴሽን ያሉ ታላቅ አላማን በመሰነቅ ለወገን ለመድረስ እና የዜግነት ኃላፊነታቸውንም ለመወጣት የሚሰሩ የበጎ አድርጎት ተቋማት ጥረት እንዲሰምር አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

‎ሚኒስቴሩ በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የቤተሰብ ደህንነት እንዲጠበቅ ብሎም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያገኙ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

Please follow and like us: