‌‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በስደተኛ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ስምምነቱን የተፈራረሙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን ናቸው።

‎‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስደተኛ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተሰጧቸውን መብቶች በተግባር እንዲጠቀሙ እና በሀገሪቱ የማህበራዊ ልማትና የደህንነት ማዕቀፎች ውስጥ ተካተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ሁለቱም ተቋማት በስደትና ተመላሽ ዜጎች ዙሪያ ከዚህ ቀደም በተናጠልና በጋራ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸው ገልፀው ቅንጅታዊ አሰራሩ መፈጠሩ የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግ ገልፀዋል። ‎ስምምነቱ ዘላቂና አካታች የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት፣ የስራ ድግግሞሽን ለማስቀረት፣ በተቋማቱ መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ስራ ለማጎልበትና ስደተኞችን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

‎‎የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ስታስተናግድ የቆየች ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀዋል። ስደተኞችን ከመደገፍ ባለፈ ወደ ልማት ተኮር ምላሽ አሰጣጥ የሚደረገውን ሽግግር በግንባር ቀደምነት በመተግበር ላይም ትገኛለች ብለዋል።‎ ‎ስምምነቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈፃሚ ለማድረግ ጠንካራ መሠረት ይጥላል፤ ሌሎች በስደተኞች ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻና አጋር አካላትንም ለማቀናጀት ያስችላል ብለዋል።

‎‎በቀጣይም ሁለቱም ተቋማት ስምምነቱን እስከታች በማውረድ ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራትን በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል።
‎

Please follow and like us: