ፋይዳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ጤና፣ የፍትህ ስርዓት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በሀገራዊ የልማት ግቦች ላይ የራሱን አወንታዊ አበርክቶ ያሳርፋል – ክብርት ሂክማ ከይረዲን

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በዕለቱ እንደገለፁት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከመታወቅም ባለፈ የሴቶች ሁለንተናዊ መብት ማስፈፀሚያ መሳሪያ መሆኑን ገልፀው ይህ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የምክክርና የንቅናቄ መድረክ ይህንኑ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስቴር መ/ቤት የሴቶችንና ህፃናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ፣ ተሣትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆንና በፍትሀዊነት ተደራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተለይም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ጤና፣ የፍትህ ስርዓት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በሀገራዊ የልማት ግቦች ላይ የራሱን አወንታዊ አበርክቶ እንደሚያሳርፍ ገልፀዋል ። ከነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የዲጂታል መታወቂያ ስርዐትም ሴቶችንና ህፃናትን ያካተተ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታል ኢትዮጵያዊ 2030 ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ዲጂታል የሚደረገው ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ከዚህ በኋላ የሚሰጡ ማናቸውም አገልግሎቶች ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አስገንዝበው የመታወቅ መብት አማራጭ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል። የተያዘው ግብ መሉ በሙሉ እንዲሳካ በቅንጅትና በትብብር በመስራት ተግዳሮቶችን በመቅረፍና ለተፈፃሚነቱ በተለይ ሴቶች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳሚናስ በላይነህ በበኩላቸው ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ የማድረግ ስራውን ለማሳካት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው መታወቂያው የሴቶችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ የእኩልነትና የማህበራዊ ፍትህን ለማፋጠን የምንንቀሳቀስበት ቁልፍም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል ።

ንቅናቄውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባባሪ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልል ለተውጣጡ የሴት አደረጃጀቶች፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መዋቅሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በዕለቱ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ጋምቤላ ክልል ለመጡ ተሳታፊዎች የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም መግለጫ፣ የዲጂታል መታወቂያ የፓሊሲና የህግ ማዕቀፍ፣ የፋይዳ መታወቂያ አካታችነትን በማጎልበት ረገድ የሚኖራቸው ሚና በሚል የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ክልሎቹም እስካሁን ባሉ ሂደቶች የገጠሙ ችግሮችንና ያሉ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተካሂዶበታል።

Please follow and like us: