‎ኢትዮጵያ የህፃናት መብቶች አፈጻጸም ሪፖርቷን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቀረበች

ኢትዮጵያ የህፃናት መብቶች ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያከናወነቻቸውን ተግባራት የሚዳስሰውን 6ኛ እና 7ኛ ጥምር ወቅታዊ ሪፖርት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ በጄኔቫ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብቶች ኮሚቴ አቅርባለች።
‎‎በዚህ መሰረት የሪፖርት ማቅረብ ሂደቱ በኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን እና በኮሚቴው ባለሙያዎች መካከል በተደረገ ጥያቄ፣ ማብራሪያ  እና ግልጽ ውይይትን ያካተተ ነበር።
‎‎በሂደቱ ወቅት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተከናወኑ የህግ፣ የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎችን እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችንና ስኬቶችን ለኮሚቴው በዝርዝር አስረድተዋል። በተለይም በአማራጭ ድጋፍና እንክብካቤ ፕሮግራሞች አፈፃፀም፣ በህፃናት ተሳትፎ፣ በህፃናት መብት ጥበቃ፣ በቤተሰብ ህግ፣ በህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር መከላከል፣ በስደተኛ ህፃናት እና በህፃናት ፍትህ አስተዳደር ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ለውይይት ቀርበዋል።

‎‎ከዚህ በተጨማሪ በጤናው ዘርፍ የጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች እና በትምህርት ተደራሽነት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች የውይይቱ ዋነኛ አካል ነበሩ። የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በሪፖርቱ ላይ ተመስርተው የተለያዩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑም ለእነዚህ ነጥቦች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል። ‎በመጨረሻም ኮሚቴው ያቀረባቸው ምክረ-ሃሳቦች በቀጣይ በኢትዮጵያ የህፃናትን መብትና ደህንነት ይበልጥ ለማስከበር እንደ መመሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ በመግለጽ ሂደቱ ተጠናቋል።
‎

 

 

Please follow and like us: