Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ፋይዳ ከምዝገባና ከመታወቅ ባለፈ የሴቶችንና የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ልዩ ትርጉም ሰጥቶ መስራትና ሃላፊነትን በተሟላ መንገድ መወጣት እንደሚገባ ተገለፀ
የፋይዳ ለኢትዮጵያ ለሴቶች የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐግብር በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በመርሐግብሩ ላይ የአፋርና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ይገኛል። የአፋር ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን አሊሳ ሀገራችን የጀመረችው የብልፅግና ጉዞ በማፋጠን ረገድ የሴቶች ተሳትፎና አስተዋፅዖ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህም የመጣንበት መንገድ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል። ሴቶች በተግባር በተሰማሩበት ሁሉ ወጤታማ መሆናቸውን በመጥቀስ የተጀመረው የብሔራዊ ፋይዳ ለኢትዮጵያ የንቅናቄ ስራው ከዳር እንዲደርስ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይሬዲን በበኩላቸው፥ ፋይዳ ከምዝገባና ከመታወቅ ባለፈ የሴቶችንና የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ልዩ ትርጉም ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ፋይዳ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች ጉዳይ ነው፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ስለሚያግዝ ሴቶችና ህፃናትን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል። እስከ ሰኔ 30 ሚሊዮን ሴቶችና 10 ሚሊዮን ህፃናትን የፋይዳ ባለቤት ለማድረግ መታቀዱን ገልፀው እንደሀገርም ሆነ እንደሴክተር የተቀመጠው እንዲሳካ የቢሮ ሃላፊዎች፣ የሴቶች አደረጃጀቶች ጨምሮ ሁላችንም ሃላፊነታችንን በተሟላ መንገድ መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ራሔል አብራሃም በበኩላቸው፥ ፋይዳ መሠረታዊ የማንነት መታወቂያ ስርዓት ለመዘርጋት፣ ሀገራችን ለጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ እና በተለያዩ አካላት የሚሰጡ ቁልፍ አገልግሎቶችን እርስ በእርስ ለማናበብና ለማቀናጀት ያስችላል ብለዋል። የተያዘው የ90 ሚሊዮን እቅድ እውን ለማድረግ የሴቶች ድርሻ የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።
