Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማዳም ይቬት ኩፐር በዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ ያለውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉብኝት አደረጉ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እና የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ የልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማዳም ይቬት ኩፐር እና ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን የዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።
ልዑካኑ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት (One Stop Centre)፣ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እና የማህፀንና ፅንስ ሕክምናን እንቅስቃሴዎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በዚሁ ጊዜ፥ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ ክስተቶች ምክንያት ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የአንድ ማዕከል፣ ጊዜያዊ ማረፊያና የማገገሚያ ማዕከላትን እንዲቋቋሙ በቅንጅት እየተሰራ እና የተቀናጀ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ረጅም ዘመን ያስቆጠረና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀው፣ ዩናይትድ ኪንግደም በተለይም ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ለማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች እያደረገች ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የማዳም ይቬት ኩፐር ኦፊሴላዊ የስራ ጉብኝትም ሁለቱ ሀገራት በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቀጣይ ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክርም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። የዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ የልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር በሆስፒታሉ በሚገኘው የአንድ ማዕከል በተለይ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እየተሰጠ ባለው የተቀናጀ ድጋፍ አገልግሎት መደሰታቸውን ተናግረዋል።
