Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ህፃናትን ከጥቃትና ብዝበዛ ለመታደግ የሚያስችል አዎንታዊ የዲጂታል አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገለፀ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ህፃናት በበይነ መረብ አማካኝነት ከሚደርስባቸው ጥቃትና ብዝበዛ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የግንዛቤና ንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ዳኞችና የፖሊስ አካላት እንዲሁም የህፃናት መብት ጥበቃና ምላሽ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል። በሚኒስቴሩ የህፃናት መብት ጥበቃና ምላሽ መስጠት ዴስክ ሃላፊ ቃልኪዳን ሽመልስ በዚሁ ወቅት፥ ጊዜው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን ጠቅሰው ይህም ህፃናት የፈጠራ ችሎታቸውን፣ ተሰጥኣቸውንና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ፣ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩና አጋዥ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እንዲሁም ተጨማሪ የትምህርት እድሎችን እንዲጠቀሙ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አንስተዋል። ሆኖም በእውቀት ላይ የተመሰረተና ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀም ልምድ ከሌለ ህፃናት ከማያውቁት ሰው ጋር ሊገናኙ፣ በአጥቂዎች እጅ ላይ ሊወድቁና በበይነ መረብ አማካኝነት ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ጥቃቶች ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡
ለረዥም ጊዜ መጠቀም በጤናና በትምህርት ውጤታማነት ላይ ከሚያስከትለው ውስብስብ ችግር ባሻገር ተገቢነት የሌላቸው ይዘቶችን ማየት በህፃናት ስነ-ተግባቦት፣ ስነልቦናና ሁለንተናዊ ስብዕና ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድርም ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የህፃናት የበይነመረብ አጠቃቀም ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግና ማስተማር ይገባል፤ ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ መምህራን፣ ማህበረሰቡና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአካቶ ትግበራ ቁጥጥርና ድጋፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ከተማ ለገሰ በበኩላቸው፥ ህፃናትን ከጥቃትና ብዝበዛ ለመታደግ የሚያስችል አዎንታዊ የዲጂታል አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። የህፃናት ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሃላፊነት አይደለም ያሉት አቶ ከተማ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ አስፈፃሚ አካላት የህጻናትን የበይነ መረብ ጥቃት ተጋላጭነት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን በእቅዳቸው አካተው ሊተገብሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የበይነ መረብ አጠቃቀምን ጨምሮ ለህጻናት መብትና ሁለንተናዊ ደህንነት መጠበቅ የሚበጁ የአሰራር ማዕቀፎችን በመቅረፅ በስራ ላይ እንዲውሉ ለማስቻል የጀመራቸውን ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
