Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶች ታዳጊ ሴቶችና የሴት ተመራማሪዎች ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከበረ
የኢትዮጵያ ሴት ተመራማሪዎች ማህበር ቀኑን በማስመልከት በሳይንስ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ ተካሄደ።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ የሴት ተመራማሪዎች ህብረት መፈጠሩና መጠናከሩ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል። በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና ምርምር ዘርፍ ጫናዎችን አልፈው ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ትልቅ ስራ ሲሰሩ ለቆዩና እየሰሩ ያሉ ሴት ተመራማሪዎችን ክብርት ሚኒስትሯ አመስግነዋል።የሴት ተማሪዎችና ተማራማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀው በቀጣይም የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን፣ ሴቶችን ለማብቃትና ወደ አመራር እንዲመጡ ለማስቻል ሚኒስቴሩ የጀመረውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና ምርምር ዘርፍ የሴት ተማሪዎችን፣ ታዳጊዎችንና ተመራማሪዎችን ተሳትፎ ከማሳደግ ጎን ለጎን በአግባቡ መደገፍ፣ ማብቃትና ወደ አመራርነት እንዲመጡ ምቹ መደላደል መፍጠር ይገባል ብለዋል። ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ መንግስቲዊና አለም አቀፍ ድርጅቶች የድርሻውን እንዲወጡም ክብርት ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል። ሴት ተመራማሪዎች ያሉትን መልካም እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ችግር ፈቺ ተግባራትን እንዲያከናውኑና ሀገራችን ለጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት እንዲረባረቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የምርምር ስነምህዳር ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ተመራማሪዎችን ለማፍራት አበክረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ሴት ተመራማሪዎች ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር አስቴር ተሾመ ማህበሩ የሴት ተመራማሪዎችን አቅም ለማሳደግና ጎልቶ እንዲወጣ ለማስቻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
