በፈንጂ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች አካታችና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማጠናከር ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሂማኒቲ ኢንክሉዥን ጋር በመተባበር በፈንጂ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ የሚያስችል ባለድርሻ አካላት ያቀፈ ፎረም ተመሰርቷል።

‎የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  ክብርት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ የፎረሙን ምስረታ ይፋ ባደረጉበት ወቅት የተጎዱትን መልሶ ማቋቋም፣ የአካል ድጋፍ ማቅረብና በመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ዉስጥ ተካታች መሆናቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ‎ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በፈንጂ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን በመደገፍ ሂደት ውስጥ፣ በአካል ጉዳተኞች መብት፣ በማህበራዊ ጥበቃ፣ በጤናና በመልሶ ማቋቋም ዙሪያ እስካሁን በተበታተነ መልኩ በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች የሚከናወኑ ተግባራትን  የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

‎‎ይህ አሰራር ግን ክፍተቶች እንዲፈጠሩና አንዳንድ አካባቢዎች ትኩረት እንዳያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። የፎረሙ ዋና ዓላማም በፈንጂ ምክንያት ተጎጂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመደገፍና መልሶ  ማቋቋም ስራን በቅንጅትና በትብብር ለመስራት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‎ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ለጋሽ ድርጅቶች እና የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የፈንጂ አደጋ ስጋትን ጨርሶ ለማስወገድ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

‎

Please follow and like us: