Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ለ34 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና 4 ክልሎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፋውንዴሽን የተበረከተለትን ድጋፍ ለ34 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና 4 ክልሎች አስረከበ።
የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላትን በማተባበር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍና በዘላቂነት አንዲቋቋሙ ለማስቻል በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የድጋፍና እንክብካቤ የሚሰጡ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለማጠናከርም ቀደም ሲል የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፋውንዴሽን ሚኒስቴሩ ለሚሰራቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገና ማህበራዊ ሃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል። ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ ያለሉየበጎ አድራጎት ተቋማትን አመስግነው ለተቋማቱ የሚደረገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ድጋፉ ለሌሎችም ተቋማት እንደሚሰጥ ጠቅሰው እንደ ሀገር የበጎ አድራጎት ስራው ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል ስርዓት የመገንባት ስራ ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ለተጋላጭ ወገኖችና የእንክብካቤ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ሁሉም ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስተዳደርና የሰው ሀብት ልማት አቶ በቀለ ያሂ በበኩላቸው፥ ፋውንዴሽኑ ሚኒስቴሩ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፤ የበጎ አድራጎት ስራውን ከማጠናከር ጎን ለጎን በሚዘረጋው የአሰራር ስርዓት መሠረት ዜጎችን በራስ አቅም በዘላቂነት ለመደገፍ በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
