Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ሰላም ሚኒስቴር ከሴቶች አደረጃጀት ጋር በመተባበር “በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ የንቅናቄ መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ስኬቶች ተመዝግበዋል። የሀገሪቱ የልማት ፖሊሲዎች ሴቶችን የለውጥ ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሴቶች በሀገር ልማት ጉልህ ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል። በኢኮኖሚ ዘርፍ ሴቶች የሀብት ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አንስተው፤ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ከነበረበት 16 በመቶ ወደ 50 በመቶ መድረሱን በማህበራዊ ዘርፍ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ጠቅሰዋል። በፓርላማ የነበረው የሴቶች ጥቂት ተሳትፎ አሁን ላይ 41 በመቶ መድረሱን ብሎም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያላቸው ተሳትፎ ግማሽ ያህል መድረሱ በፖለቲካ ዘርፍ ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል። በመሆኑም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። በሀገራዊ ምርጫ የሴቶች ሚና መተኪያ የሌለውና አስፈላጊ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሴቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ እና የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ክብርት ዘሃራ ዑመድ እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጋራ ብልፅግናንና አካታችና የሴቶችን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የሴቶችን ግንዛቤ በማሳደግ የማብቃት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሴቶች ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል። የዛሬው መድረክ ከጥር 12 ቀን እስከ የካቲት 12 ቀን 2018 ዓም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ የማጠቃለያ መድረክ ሲሆን ለአንድ ወር በቆየው መድረክ 10 ሚሊየን በላይ ሴቶችን ማወያየት መቻሉን ተናግረዋል። በተጨማሪም የደም ልገሳ፣ የማዕድ ማጋራት መርሃግብርን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ብሎም የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሴቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
በመርሃግብሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ እና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሴቶች አደረጃጀት አባላት ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
