‎የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባውን ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት አስመርቆ ቁልፍ አስረከበ

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባውን ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት አስመርቆ ቁልፍ አስረክቧል።
‎‎በመርሃ ግብሩ የተገኙ የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ መንግስት በሰው ተኮር ፕሮግራሞች ዜጎች ምቹ በሆኑ አከባቢዎችና የመኖሪያ መንደሮች እንዲኖሩ አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ‎በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገነቡ 5 ዘመናዊ ቤቶች መኝታ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሽንት ቤት፣ ሻወር ቤት እና የማብሰያ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን በተጨማሪም 24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ማስጠቀም የሚያስችል የሶላር ሲስተም የተገጠመለት እንዲሁም በመሠረታዊ ቁሳቁሶች የተሟላና የአረንጓዴ ስፍራዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰዋል። ‎የመኖሪያ ቤት ግንባታው 3 አባዎራዎችንና 2 እማወራዎችን በአጠቃላይ 20 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጡሩም ባሻገር በአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም በራስ አቅም የማህበረሰብ ችግርን መፍታት እንደሚቻል የተማርንበትን አጋጣሚ ፈጥሯል ሲሉም ገልፀዋል።

‎ሆኖም የማህበራዊ ልማት ስራዎችን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ከሚገኘው ብርቱ ጥረት ባሻገር የማህበረሰብ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም አንስተዋል። ‎የተለያዩ ግለሰቦችንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን ወደ መሬት ማውረድ እንደሚገባ፣ የኮሪደስ ልማትና መሠል የበጎነት ስራዎችንም አጠናክሮ ማስቀጠልና መንከባከብ እንደሚያስፈልግም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአፅዕኖት አሳስበዋል።

Please follow and like us: