‎በኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ስርአትን ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር የሚያስችለው የብሔራዊ የማህበራዊ ዲጂታል መዝገብ (National Social Registry) የዳሰሳ ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ሆነ

ይህ መዝገብ በተለያዩ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ስር ተበታትነው የሚገኙ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል በማደራጀት፣ ድጋፍ በቀጥታ ለሚገባቸው ዜጎች እንዲደርስ የሚያደርግ, የሀብት ብክነት የሚቀንስ እንዲሁም ፈጣን የማህበራዊ ጥበቃ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።

‎በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በጥናቱ ይፋ ማድረጊያ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለማህበራዊ ዲጂታል መዝገብ ስራ ልዩ ትኩረት በሰጠበት ወቅት ይህ ጥናት መጠናቀቁ ውጤቱን ለስራቸው ምቹ ግብዓት እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ማህበራዊ ደጅታል መዝገብን በማበልፀግ እንዲሁም የዳታ አጠቃቀም ፖሊሲ መዋቅርን በማዘጋጀት ሚኒስቴሩ በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣኖች መካከል አንዱ የሆነውን የማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚዎች መረጃ በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት ስራን እየሰራ ይገኛል።

‎‎ይህ አዲስ የዲጂታል መዝገብ ከፋይዳ (Fayda) ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የሙከራ ትግበራ እንደተጠናቀቀ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባ ይጠበቃል። ዲጂታል መዝገቡ አሰራርን ለማቀላጠፍና የማህበራዊ ድጋፍ መረጃን በአግባቡ ለማቀናጀት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተመላክቷል። ይህ የዳሰሳ ጥናት የተከናወነው በአለም ባንክ ሲሆን ክብርት ሚኒስትር ዲኤታዋ፣ ባንኩ ይህንን ጠቃሚ ጥናት ለማከናወኑ እንዲሁም ለማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Please follow and like us: