Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች መደገፍና ለስኬት እንዲበቁ ማገዝ ይገባል – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አለም አቀፉ የዳውን ሲንድሮም ቀን “ብቸኝነትን በጋራ እናሸንፋለን!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።
በዚሁ ጊዜ “የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የፈጣሪ ቁጣ አይደለም” ያሉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መደገፍና ለስኬት እንዲበቁ ማገዝ እንደሚገባ ገልፀዋል። ነጋቸው ብሩህ እንደሚሆን በማመን እንደዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ፍቅር የአእምሮ እድገት ውስንነት ማህበር ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ለህጻናቱ እና ለቤተሰቦቻቸው የተስፋ ብርሃን በመሆኗቸውም ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል። ጥረታቸው ውጤታማ እንዲሆንም ሚኒስቴሩ የበኩሉን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በተሳሳተ ግንዛቤ ቤት ተዘግቶባቸው የዛሬውን የተስፋ ብርሃን ሳያዩ የቀሩ ህጻናት መኖራቸውን ጠቅሰው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን እንዳይደብቁ፣ በኩራት እንዲያቀርቧቸው እና በክብር ማህበረሰቡም እንዲቀበላቸው መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ክብርት መቅደስ ዳባ ናቸው። የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፥ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸውን ህጻናትም ሆነ እነሱን ለማገዝ ፋውንዴሽኑን ለማጠናከርና ሌሎችንም ለማስፋፋት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
