Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ከአማራጭ ህፃናት ክብካቤ እና ድጋፍ ተቋማት አድገው በወጡ ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከየአማራጭ እንክብካቤ አድገው የወጡ ማህበራት ጥምረት ጋር በመሆን ጥምረቱ በአማራጭ እንክብካቤ አድገው በሚወጡ ወጣቶች እና የአማራጭ ድጋፍ እንክብካቤ መመርያ ዙርያ ለሚዲያ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄዷል።
በመርሀ-ግብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህፃናት ድጋፍ፣ አገልግሎት ማስፋፍያና ማጠናከርያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሀሰን መሀመድ፤ ታዳጊ ወጣቶች ከአማራጭ ክብካቤ አገልግሎት ለመውጣት በሚደረገው ዝግጅትና ድህረ ክብካቤ ወቅት ደረጃውን የጠበቀ፣ ግልጽና ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት ለሥነልቦናዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን አንስተዋል። ደረጃውን የጠበቀ ግልጽና ወጥነት ያለው ዝቅተኛ አገልግሎት መስጫ መስፈርት በማዘጋጀት ከአማራጭ ክብካቤ የሚወጡ ታዳጊ ወጣቶች በዘላቂነት እራሳቻውን እንዲችሉ ማስቻል ዋነኛው ጉዳይ ነው በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። አክለውም የሚዲያ አካላት ወጣቶቹ እንደማንኛውም ዜጋ መብታቸው ተከብሮ ውጤታማ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት በመገንዘብ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ በማለት አስገንዝበዋል።
የአማራጭ እንክብካቤ አድገው የወጡ ማህበራት ጥምረት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ አበራ በበኩላቸው ይህ ጥምረት በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰብ ውጪ በሆኑ አማራጭ እንክብካቤዎች ውስጥ አድገው ለሚወጡ ወጣቶች መብት፣ ጥቅም እና ደህንነት መከበር ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ጥምረቱ በአማራጭ እንክብካቤ አድገው በሚወጡ ወጣቶች እና የአማራጭ ድጋፍ እንክብካቤ መመርያ ዙርያ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
