Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማህበረሰብ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስን እና የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት እንዲመራ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የሐመር ወረዳ ሻንቆ ቀለማ ቀበሌ ነዋሪዎች ህያው ማሳያ ናቸው -ክብርት ሒክማ ከይረዲን
ይህ የተገለፀው በኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ ሻንቆ ቀለማ ቀበሌ በመገኘት በሴንተር ኦፍ ኮንሰርን”COC” የበጎ አድራጎት ድርጅት የተሰሩ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው።
ልዑካን ቡድኑ በሐመር ወረዳ ሻንቆ ቀለማ ቀበሌ በመገኘት በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተገነባውን የህፃናት መጫወቻ ስፍራ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያ ቁሳቁሶች የተሟላለትና ለህፃናት ምቹና ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ተዟዙረው ተመልክተዋል። ትምህርት እየተከታተሉ ያሉ ህጻናት በመማር ማስተማር ሂደቱ ያሉበትን ደረጃ በምልከታ አረጋግጠዋል። እንዲሁም የወጣት ሴቶች ላይ ከመጤ ልማዶች እንዲጠበቁ በተሰሩ የግንዛቤ ስራዎችና በመጡ ውጤቶች ዙሪያ ከማህበረሰቡ ጋር ተወያይተዋል በተጨማሪም ከፍተኛ አመራሩ ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከሴቶች ተወካዮች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚሁ ጊዜም፥ መንግስት የመሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለሰጠው ትኩረት የአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋናን አቅርበዋል። አሁን ያሉ አበረታች ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የአርብቶ አደር አካባቢውን የአኗኗር ዘዬ ያገናዘበ በተለይም በትምህርት፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና እና መሰል የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እዲስፋፉና መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የማህበረሰብ ተወካዮች ጠይቀዋል። የቀበሌው ማህበረሰብም በግብረሰናይ ድርጅቱ የተሰሩ የህፃናት መማሪያ ትምህርት ቤት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉ አካላትን ከልብ አመስግነው በቀጣይም ትምህርት ቤቱ አጥር እንዲኖረው እና ሌሎች ቀበሌዎች ላይም ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ እንዲያደርጉ በአፅንዖት አንስተዋል። ይህንንም ተከትሎ ከማህበረሰቡ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ብርትት ሒክማ ከይረዲን ከቅርብ አመታት በፊት በአካባቢው ስለትምህርት፣ ጤናና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ስለተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አስታውሰው ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ተቋማት እንዲልክ በጠየቅን በአጭር ጊዜ ውስጥ ልጆቹን በመላክ የትምህርት ተቋማት እጥረት እንዳለ ማንሳቱ ትልቅ እመርታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማህበረሰብ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስን እና የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት እንዲመራ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የሐመር ወረዳ ሻንቆ ቀለማ ቀበሌ ነዋሪዎች ህያው ማሳያ ናቸው ሲሉ ሚንስትር ዴኤታዋ አክለዋል። ”COC” የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እየተገበረ ያለው ፕሮግራም በዋናነት ህጻናት ከማናቸውም አይነት ጥቃት ነጻ የመሆንና ጥራት ያለው የቅድመ መደበኛ ትምህርት የማግኘት/የመማር መብታቸው እንዲረጋገጥ አስተዋጾኦ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ላለው ተግባርም ክብርት ሒክማ ምስጋናቸውን ቸረዋል። የወጣቶች ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ በበኩላቸው፥ የሻንቆ ቀለማ ወጣቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተላቀው የስራ ፍላጎት ላይ የመጣው ለውጥ አበረታች እንደሆነ ገልፀዋል። ወጣቶቹ ሰርቶ ለመለወጥ ያላቸውን ፍላጎት በተሟላ መንገድ ከመመለስ አኳያ በተለይ ከመስሪያ ገንዘብ እና ከክህሎት ስልጠና እንዲሁም በሚፈልጉት የስራ መስክ ላይ ለመሰማራት የሚገጥማቸውን ማነቆዎች በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት እንደሚሰራ ለወጣቶቹ አረጋግጠውላቸዋል። በተጨማሪም የቡድኑ አባላት በቱርሚ ሆስፒታል እና ሻንቆ ጤና ጣቢያ በመገኘት እየተሰጠ ያለውን የአንድ ማዕከል እና የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ አገልግሎት ጎብኝተዋል።
ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር በመተባባር እየተገበረ ያለው ፕሮግራም በዋናነት ህጻናት ከማናቸውም አይነት ጥቃት ነጻ የመሆንና ጥራት ያለው የቅድመ መደበኛ ትምህርት የማግኘት/የመማር መብታቸው እንዲረጋገጥ አስተዋጾኦ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።
