‎በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሴቭ ዘ ችልድረን መካከል በህፃናት መብትና ጥበቃ ስትራቴጂያዊ ስራዎች የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ (Save the Children Ethiopia) ጋር በሀገሪቱ የህፃናትን መብት ለማስከበርና የጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል፡፡

‎‎የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፥ ሚኒስቴሩ እንደሀገር የህፃናትን ሁለንተናዊ እድገት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማስክበር አኳያ በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።‎በተለይ የቀዳማዊ ልጅነት እድገትን በማስፋፋትና በማጠናከር ረገድ ያሉ ጅምር ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት፣ ትርጉም ያለው የህፃናት ተሳትፎ በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። ‎በተጨማሪም የፖሊሲዎችን አፈፃፀምና አተገባባርን በመቃኘትም በዘርፉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የህፃናት ጥበቃ ስርዓቶችን የመዘርጋት አንዲሁም ተገቢውን ድጋፍና ምላሽ እንዲያገኘ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‎ስምምነቱም በዋናነት አጋርነት፣ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በማድረግ ለህፃናት ደህንነት በጋራ መስራትን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‎የሴቭ ዘ ችልድርን ኢትዮጵያ ካንትር ዳይሬክተር ሚስ ድራጋና ስትሪንች በበኩላቸው፥ ባለፉት አመታት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በህፃናት ጥበቃ ተግባራት የሚያስፈልግ የህፃናት ምላሽ ሰጪ በጀት በሁሉም ዘንድ ታሳቢ እንዲደረግ በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

‎‎የህፃናት ትምህርትና ምላሽ ሰጪ አገልግልሎቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር ህፃናት መብት፣ ጥበቃና ተጠቃሚነት ላይ ስርዓት መዘርጋት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም በመግለፅ ሴቭ ዘ ችልድረን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል፡፡‎ስምምነቱ የሚቆየው እ.ኤ.አ ከ2026 እስከ 2028 ሲሆን በዋናነት የህፃናት ጥበቃ ስርዓትን ማጠናከር፣ በህፃናት ዘርፍ የተዘጋጁ የአሰራር ማዕቀፎችን በተግባር ላይ ማዋል፣ የተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናት ማካሄድ እና የህፃናትን መብትና ተሳትፎ ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩር ተጠቁሟል፡፡‎በመሆኑም ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል የድርጊት መርሀ-ግብር  በማዘጋጀት አፈፃፀም በበላይነት የሚከታተልና በየስድስት ወሩ የሚገናኝ የጋራ ስቲሪንግ ኮሚቴ የሚቋቋም ሲሆን፣ ይህም በሀገሪቱ ለሚገኙ ህፃናት የተሻለ መብት ጥበቃ፣ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበርክት በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
‎

Please follow and like us: