በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት በተዘረጋው የተቀናጀ አሠራር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይረዲን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው የብሔራዊ አስተባባሪ አካል አብይ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት እንደገለጹት፤ መንግሥት ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የትብብርና የቅንጅት ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ።

በዚህም ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ ሴክተሮችን በማቀናጀት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ የፍትሕ፣ የጤናና ሌሎች ድጋፎችን በአንድ ላይ የሚሰጡ የአንድ ማዕከል (One Stop Centers) ማስፋፋቱን ገልፀዋል። ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም አሁንም ጥቃት እንዳይደርስና ጥቃቶችን መቀነስ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን ለማሳካት ሁለተኛው ብሔራዊ ስትራቴጂ ወጥቶ ትግበራ መጀመሩንና ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል ። በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለተጎጂዎች የሚሰጠውን ድጋፍ ለማሻሻል በፍትሕ ተቋማት የጾታዊ ጥቃት ወንጀሎች ምርመራና የክርክር አደረጃጀትን የማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል ። መንግሥት እንደ ባለድርሻ አካል ጥቃትን ለመቀነስ ለጥቃት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን በመለየት አዳዲስና ዘመኑን የዋጁ ስልቶችን በመንደፍ ምላሽ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል::

ለዚህም እንደ ማሳያ በ96 የፓይለት ሳይቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ዲጂታል የጾታዊ ጥቃት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት (GBVIMS+) የክትትልና የምላሽ አሰጣጥ ሥራውን ይበልጥ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ እንደሚያደርገው ታምኖበታል ።የብሔራዊ አስተባባሪ አካሉ በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ጥቃቶችን ለመከላከልና የሕፃናትን ፍትሕ ለማረጋገጥ ያስችለው ዘንድ በድጋሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአሠራር ስርዐቱን በማሻሻል አዳዲስ ተቋማትን በማካተት የመግባቢያ ሰሰነድ በማፅደቅ ወደ ስራ ገብቷል። በዕለቱ የብሔራዊ አስተባባሪው በቀጣይ ጊዜያት የሚሠራቸውን እቅድ የፀደ ሲሆን ረቂቅ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መረጃ አያያዝ ሥርዐት (GBVIMS+) እንዲሁም በሴቶቾ እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የመረጃ ስርዓት (CRIMS)ን የማስተዋወቅ ስራ ተሠርቷል።

Please follow and like us: