Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ቤተሰብ የቋንቋ፣ የባህልና የታሪክ ማስተላለፊያ ድልድይ በመሆን የትውልድን ማንነት የመጠበቅና የጋራ ሀገራዊ ትርክትን የመገንባት ታላቅ ኃላፊነት አለበት- ክብርት ሁሪያ አሊ
በዛሬው እለት የተከበረውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፣ እንደገለፁት ቤተሰብ ለማንነታችን መሰረት፣ ለጥንካሬያችን ምንጭ እና ለሀገራዊ አንድነታችን ምሰሶ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ቤተሰብ የቋንቋ፣ የባህልና የታሪክ ማስተላለፊያ ድልድይ በመሆን የትውልድን ማንነት የመጠበቅና የጋራ ሀገራዊ ትርክትን የመገንባት ታላቅ ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን በቤት ውስጥ የሚለመድ ሰላማዊ ውይይት፣ መቻቻልና የሌሎችን መብት የማክበር እሳቤ ለዘላቂ ልማትና ለፖለቲካዊ መረጋጋት ምቹ ሁኔታንም እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቤተሰብን መጠበቅ ማለትም ሀገርን ከመልካም እሴቶች መሸርሸርና ከማህበራዊ ቀውሶች መጠበቅ እንደሆነ በመረዳት ቤተሰብ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት መሰረት በተፈጥሯዊ ተቋምነቱ ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ጥበቃ የማግኘት መብት ያለው በመሆኑ፣ ይህንኑ ጥበቃ በተግባር ለማዋል ተቋማዊ የማስተባበር ስራዎች በመከናወን ላይ እንዳሉ ጠቁመዋል ።
በኢኮኖሚው ረገድም ቤተሰብ በከተማም ሆነ በገጠር ዋነኛው አምራች ኃይል በመሆን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ወደር የሌለው ሚና እንደሚጫወት ገልፀው ጠንካራ የቁጠባና የኢንቨስትመንት ባህል ያላቸው ቤተሰቦች የሀገርን የካፒታል አቅም ከመገንባታቸውም በላይ፣ በቤት ውስጥ የሚጀመር ስራ ወዳድነትና ታማኝነት የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ ቀዳሚውን ድርሻ እንሚይዝ አስታውቀዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ ቤተሰብ በኢኮኖሚ የጠነከረ፣ በማህበራዊ ግንኙነቱ የተሳሰረና በስነ-ምግባር የታነፀ እንዲሆን በማድረግ ለፀናችና ለበለፀገች ሀገር ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የዘንድሮው የቤተሰብ ቀን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ኸልፕ ኤጅ ኢትዮጵያዊ ጋር በመተባበር “በመልካም ቤተሰብ፣ መልካም ትውልድ፣ ለፀና ሀገር!” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል።
