Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባለፉት የለውጥ አመታት ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት በአማራጭ የእንክብካቤ ፕሮግራሞች መደገፍ ተችሏል

ከለውጡ ወዲህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት በተለያዩ የሃገር ውስጥ አማራጮች እንዲደገፉ ማድረግ ተችሏል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናትን በተለያዩ አማራጮች ለመደገፍ የሚያስችል ሰፊ ስራ በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በአማራጭ ፕሮግራሞች የተደገፉ ህፃናት ቁጥር ከለውጡ በፊት ከነበረው 12 ሺህ 058 ወደ 2 ሚሊዮን 380 ሺህ 622 ሊደርስ ችሏል።
ህፃናቱ በማህበረሰብ አቀፍ የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ፣ በተቋማት የ1% ስፖንሰርሺፕ ድጋፍ፣ በፎስተር ኬር፣ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርገዋል። በሌላ በኩል መንግስት ለትውልድ ግንባታ በሰጠው ትኩረት የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት ክብካቤ ፕሮግራም/ECD/ መተግበሩን ተከትሎ ከለውጡ በፊት የነበረው 350 የህፃናት መዝናኛና የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ወደ 5 ሺህ 602 ከፍ እንዲሉ ተሰርቷል።
3 ሺህ 776 የህፃናት ማቆያዎች ተቋቁመው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉም ሌላው ተጠቃሽ እመረታ ነው። ሚኒስቴሩ ወደፊትም የሕፃናትን ሁለንተናዊ መብትና ማህበራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት የሚሰራቸው ተግባራትን የሚያጠናክር ሲሆን በተለይም ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን በሃገር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ አማራጮች ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
