‎በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የመረጃ ምዝገባና አስተዳደር ስርዓት (CAEC-RIMS) የማልማት ስራ ተጠናቆ ወደ ሙከራ ትግበራ ሊሸጋገር ነው

‎የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመረጃ ምዝገባና አስተዳደር ስርዓትን(CAEC-RIMS) ለመተግበር የሚያግዙና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡

‎የግብዓት ድጋፍ ርክክብ በተደረገበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ የመዋቅር ለውጥ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ተቋማት ተቀራርበው በጋራ ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበትን ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ስለሚገባ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ተደራጅቶ የሚመለከታቸው አካላት በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግ ሲስተም የለማ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከጥቆማ ጀምሮ እስከ ምርመራና ክስ ያሉ ሂደቶችን አጠቃላይ መረጃ አደራጅቶ መያዝ የሚያስችል ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻል የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ‎በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ትብብር መልማት የቻለው በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የመረጃ ምዝገባና አስተዳደር ሥርዓት (CAEC-RIMS) የአንድን ወንጀል ሁኔታ ከጥቆማ ጀምሮ አጠቃላይ ሂደቱን አጠናክሮ መረጃን ለመያዝ፣ ክትትል ለማድረግ ብሎም የመዛግብት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ከምርመራ አንጻር ሥራዎችን በአጭር ጊዜና በውሱን የሠው ሀይል ለማከናወን ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡

‎‎በመርሃ-ግብሩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች አጠቃላይ መረጃን ማጠናከር የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅምን አሟጦ በመጠቀም የወንጀል መከላከል ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፣ የለማው ሲስተምም በዋነኛነት በአዲስ አበባ ውስጥ በሁለት ክፍለ ከተሞች ለሙከራ ተግባር ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከፍ ሲልም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚተገበር ተጠቁሟል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የተማከለና ዲጂታል የፍትሕ ሥርአትን እውን ለማድረግ ባቀደው መሰረት በአጠቃላይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መረጃ በሚመለከት የምርመራ እና የክስ ስርዓቱን መምራት የሚያስችል ዘመኑን የሚመጠን ቴክኖሎጂ በመተግበር ዲጂታላይዜሽንን የሚጠቀም የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Please follow and like us: