Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
“ያለንን ውስን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል” -ክብርት ሁሪያ አሊ
የአምስተኛው ምዕራፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (PSNP) የመጨረሻው ዓመት መጠናቀቅን ተከትሎ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል ።
በዕለቱ የሚኒስቴሩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት ያለንን ውስን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግስት የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን ግልጽ የመመልመያ መስፈርቶችን በማውጣት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመቀነስ የምናከናውናቸውን ዘርፈ-ብዙ የመከላከል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል ። አሁንም በአካል ጉዳት፣ በእድሜ መግፋትና በፅኑ ህመም ምክንያት ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነቶች የተዳረጉ ዜጎችን ለመደገፍና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በመንግስት በኩል ይበልጥ ተጠናክረው እንዲሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከአራተኛው ዙር ጀምሮ የቋሚና ጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዶ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም ሂደት ውስጥ ተቋማዊ አቅምን ከማሳደግ ባለፈ በተጠቃሚዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል ። ነገር ግን መንግስት ከሚሠራቸው ስራዎች በተጨማሪ የባለድርሻ አካላት ሚና ዜጎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮችና የማህበረሰብ አደረጃጀቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የተደራሽነት፣ አቅም ግንባታ፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስር እና ሀብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ፦ ፕሮግራሙ በእነዚህ አበይት ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች ከቀጥተኛ ድጋፍ ባሻገር ተጨማሪ የፋይናንስ፣ የዓይነትና መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል። በመድረኩ ላይ የክልል የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በዕለቱ የክልሎችን የዕቅድ ክንውን በዝርዝር በመገምገም፣ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ድክመቶችን በማስተካከያ እርምጃዎች በማረም በቀጣይ የፕሮግራሙን አጠቃላይ አፈጻጸም ማሻሻልና ወደ ስድስተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር ጠንካራ መሠረት መጣል ዋነኛ አላማው መሆኑ ተጠቁሟል።
