ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የእንክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፋውንዴሽን የተበረከተለትን ልዩ ልዩ የቁሳቁስ ድጋፎችን ለ15 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ።

‎የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን በራስ አቅም ለመደገፍና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ቀደም ሲል የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል። በዛሬው ዕለትም የተደረገው ድጋፍም የጥረቱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ ያለ የበጎ አድራጎት ተቋማትን አመስግነው ለተቋማቱ የሚደረገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

‎‎እንደ ሀገር የበጎ አድራጎት ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል ጠንካራ ስርዓት የመገንባት ስራ ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ‎ለተጋላጭ ወገኖችና የእንክብካቤ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። ‎በዛሬው ዕለት በአካል ጉዳተኞች፣ በስደት ተመላሽ ዜጎችና በአረጋውያን ዙሪያ ለሚሰሩ 15 ተቋማት ድጋፉ የተደረገ ሲሆን የተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን በርክክቡ ወቅት ገልፀዋል።
‎

Please follow and like us: