Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ተጎጂዎችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ የጋራ ቅንጅትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራው የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃና ድጋፍ የስራ ቡድን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወ/ ሮ ሁሪያ አሊ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል፣ ተጎጂዎችን መጠበቅና ተመላሾችን መደገፍ ከተቋም የዘለለ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል ላይ ያተኮረ ስራ በማጠናከር ችግር ደርሶባቸው የሚመለሱትን ለመደገፍ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የስራ ቡድኑ አባላት ጥራት ያለውን መረጃ በማደራጀት፣ የመረጃ ልውውጥን በማጠናከርና የስራ ድግግሞሽን በመቀነስ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ የአለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት (IOM) የጥበቃ ዘርፍ ሲኒየር ፕሮግራም ኦፊሰር ሜሞሪ ምዋሌ በበኩላቸው፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በሴቶች፣ በህጻናትና በተጋላጭ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመቅረፍ የመንግስት ተቋማት፣ የአጋር ድርጅቶችና የማህበረሰቡን የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ብለዋል። ለዚህም የአለም የፍልሰት ድርጅት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሁሉም አጋሮች ጋር በመተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት በጋራ እንደሚሰራና ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
