የህፃናት ሁለንተናዊ እድገት፣ ክብካቤና የጥበቃ ስርዓት ማጠናከር ነገ ሀገራቸውን የሚያሻግሩና የተሻለ ስነ-ምግባር የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት መሠረት መሆኑ ተገለፀ።

በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓሉ በአህጉር ደረጃ “ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ህጻን ንጹህ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን (WASH) አቅርቦትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል፣ በሀገራችን ደግሞ “የተጠበቁ ህፃናት ለበለፀገ ትውልድ!” በሚል መሪ ቃል ህጻናትንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ በርካታ አስተማሪ ፕሮግራሞች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።

ይህ ሀገራዊ መሪ ቃል በሁሉም ዘርፍ የህፃናት ሁለንተናዊ እድገት፣ ክብካቤና የጥበቃ ስርዓት ማጠናከር ነገ ሀገራቸውን የሚያሻግሩና የተሻለ ስነ-ምግባር የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት መሠረት መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። የበዓሉን ግቦች መነሻ በማድረግ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ሲደረግና ተጨባጭ ውጤቶች ሲገመገሙ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት በትምህርት ቤቶችና ጤና ኬላዎች ህጻናትን ያሳተፉ የማህበረሰብ አቀፍ የጽዳት ዘመቻዎች መካሄዳቸውን፣ ሞዴል ትምህርት ቤቶች ተለይተው እውቅና ማግኘታቸውን እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ለህፃናት ምቹ፣ ጽዱ እና ከጥቃት ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን በስፖንሰርሺፕ፣ በአደራ ቤተሰብና በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ የማድረግ እና የህጻናት የፋይዳ መታወቂያ እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎች በትኩረት መከናወናቸውን ገልጸዋል። ህጻናትን ለነገው ሀገር ግንባታና ኃላፊነት ብቁ ተረካቢ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የህጻናት ፓርላማ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ መደረጉን፣ የጥያቄና መልስ ውድድሮችና የፈጠራ ኤግዚቢሽኖች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

ህጻናቱ የሀገር ፍቅር፣ ባህልና እሴቶቻቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ለማድረግ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲጎበኙ መደረጉም ታውቋል። ይህ መርሃ ግብር ህጻናቱ ነገ ለሀገር ግንባታ ሂደት ከህዝባቸው የሚረከቡትን ኃላፊነት በቀጣይነት ለማስቀጠል ጉጉትና መነሳሳት እንደሚፈጥርባቸው ሚኒስትሯ አስረድተዋል። የሀረሪ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ክብርት ሮዛ ዑመር በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር ህፃናትን ማዕከል ያደረጉ ፕሮጀክቶች በተመረቁበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።የክልሉ መንግስትም የህፃናትን መብትና ደህንነት ማሰጠበቅ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆን ገልፀዋል።

Please follow and like us: